አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ በማለት ሊቃውንት ይጠሩታል።አባጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ "ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ፤ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ" ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ በዚህ ጊዜ ዐፄ ዳዊት ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ ዕዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን፤ መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡
የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡፡ "እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ አልዓዛርን የት ቀበራችሁት? ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?"ሲል የመከራከርያ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ሊቃውንቱም "እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ" ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደርጎ በአልጋ ላይ ሆኖ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ የቀረበውን ጥያቄ በነገሩት ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ሲል መለሰ፡፡ "እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ በቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? ይህን መልስልኝ እያሉ የጥያቄ ዓይነት ባሽጎደጎዱለት ጊዜ አይሁዳዊው መልስ
አጥቶ ዝም አለ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡
ምንጭ መጽሐፈ ምሥጢር
ና ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
Comments
Post a Comment