🌾🌾አጭር_አስተማሪ_ታሪክ 🌾🌾✨
🥀ልጅቷ ሥራ የላትም ፣ ከመኖሪያዋ አጠገብ ካለው የመድኃዓለም ቤተክርስቲያን ዘወትር እየተገኘች ልመናዋ ሥራ ስጠኝ ብቻ ከሆነ ሰንብታለች፡፡ በነጋ በጠባ ቁጥር “እባክህን አምላኬ ውዬ የምገባበት ሥራ ስጠኝ እያለች” እያለች ትጸልያለች፡፡ አንድ ቀን ቤተክርስቲያን ደርሳ ወደ ቤቷ ስትመለስ ከአንድ መሥሪያ ቤት አጠገብ ትደርስና የተለጠፈ የሥራ ማስታወቂያ አይታ ቆማ ማንበብ ትጀምራለች፡፡ የሥራው ዓይነት እና የትምህትቱ ደረጃ ሁሉ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡
🥀ሁሉም እሷ ልታሟላ የምትችለው መስፈርት ነበር፡፡ ደሞዙም አንድ ሺህ ብር ይላል፡፡የመሥሪያ ቤቱ ለመኖሪያ ቤቷ ቅርብ መሆን፣ የትምህርት ደረጃ መስርቱ ከእርሷ የትምህርት ደረጃ ጋር መመሳሰል፣ የመነሻ ደመወዙም ቢሆን ይህ ሁሉ ተደምሮ የመቀጠር ጉጉቷን ከፍ አደረገው፡፡ ይኹን እንጂ ከሌሎች ተመዝጋቢዎች ጋር መወዳደር ግድ ስለሆነ የማለፍና ያለማለፍ ጉዳይ እንዳለ ስትረዳ በጣም ተጨነቀች፡፡ ስለዚህ ተመዝግባ ስታበቃ ወደ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አቅንታ “እባክህን ይህን ፈተና አሳልፈኝና የሥራውን እድል ስጠኝ” ስትል ተማጸነች፡፡ ሁሉም አልፎ ውጤት የሚለጠፍበት ቀን ደረሰና በናፍቆትና በጉጉት ታጅባ ታነብ ለማንበብ ሄደች፡፡ውጤቱ ግን የእሷን ማለፍ የሚያረጋግጥ አልነበረም፡፡ የእሷ ስም የለም ያለፉት ሌሎች ናቸው፡፡ ምንም ሳትናገር ወደ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሮጠች፡፡ እዚህም እንደደረሰች “መድኃኔዓለም ታዘብኩህ” ስትል የምሬት ድምጽ አሰማች፡፡
🥀ይህ በሆነ በሳምንቱ ሌላ ማስታወቂያ በሌላ መ/ቤት ወጣ፡፡ ደመዎዙ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ነበር፡፡ ይህን ስታይ እንደመጸጸት አለችና “የእኔመድኃኔዓለም ለካስ ይሄ እንደሚሻል አውቀህ ነው ያኛው እንዲያልፈኝ ያደረከው፣ እባክህን ይቅር በለኝ የአፌን አትቁጠርብኝ ይህን ግን እንዳትከለክለኝ አደራ” ስትል ተማጸነችና ተመዝግባ ውድድሯ ጀመረች፡፡ ሁሉም አልቆ ውጤት ሲለጠፍ አሁንም የእሷ ስም የለም፡፡ ያለፉት ሌሎች ናቸው፡፡ አሁን በጣም አዘነች፡፡ በሃይማኖቷ ላይ ያላት ተስፋ ሲሟሽሽ ተሰማት፡፡ በረዶ እንደወረደበት ሰው የክርስትና ወኔዋ ቀዘቀዘ፡፡ ጊዜ ሳታባክን ወደ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሄደችና “አሁንስ በጣም ታዘብኩህ” ስትል እሱ የሰጣትን ምላስ እሱው ላይ ዘረጋችው፡፡
🥀በዚህ ሁለት ሳምንታት አለፉና አንዲት ጓደኛዋ አንድ መሥሪያ ቤት የሥራ ማስታወቂያ መለጠፉን ነግራት አልመዘገብም ብላ በማኩረፏ በብዙ ጉትጎታ ከቦታው ደረሰች ማስታወቂያውን ስታነበው ሁሉም መረጃ ከሷ ጋር የሚሄድ ሲሆን ደሞዙም ከመጀመሪያው በሁለት እጥፍ ጨምሮ ሦስት ሺህ ብር ይላል፡፡ ከሚቀር እስኪ ልሞክረው ብላ ተመዘገበች፡፡ ተገቢውን ሁሉ አድርጋ የመጨረሻ ውጤት የሚለጠፍበት ቀን ከስፍራው ተገኘች፡፡ አሁን ስሟ አንደኛ ተራ ቁጥር ላይ ተለጥፏል፡፡ በከፍተኛ ብቃት ማለፏን ስታይ ዕንባዋ በዐይኗ ግጥም አለ፣ ሁለቱን ዐይኖቿን
🥀 ስትጨፍናቸው ቋ ጥረው የያዙትን የደስታ ዕንባ በጉንጮቿ ላይ ከለበሱት፡፡ ቃል ማውጣት አልቻለችም እየበረረች ወደ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን መጣችና እየተንቀጠቀጠች ከታቦቱ ፊት ቆማ ለአፍታ ውስጧን አዳመጠች፡፡ ውስጧም አምላኳን በዚሁ ቦታ ተገኝታ ታዘብኩህ ስትል እንዳማረረችው አስታወሳት ያኔ “የኔ መድኃኔዓለም ታዘብከኝ አይደል?” አለች ለራሷ ብቻ በሚሰማ ድምጽ በቀስታ፡፡
🥀እኛስ በክርስትና ውጣ ውረድ በማይገባን መዓረግና በሌለን አቅም መድኃኔዓለምን ስንት ጊዜ ታዝበነው ይሆን? አሁን እኛ እሱን ለመታዘብ ብቃቱ አለን ? እሺ ይሁን እሱስ እኛን አንድ ጊዜ ከፍ አንድ ጊዜ ዝቅ እያልን በክርስትና ጉዞ ብልጭ ድርግም በማለት ስንጓዝ ስንት ጊዜ ታዝቦን ይሆን ለማንኛውም አይደለም እግዚአብሔርን ሰውንም እንኳን ቢሆን ለመታዘብ አንቸኩል ያ ሰው እኛንም ሊታዘበን ይችላልና፡፡
🥀የሰራዊትጌታ ታጋሾች ያድርገን።
....አሜን....
Comments
Post a Comment