የስሜት ሕዋሳቶቻችንና ክርስትና መምህር ቢትወደድ ወርቁ ሰው በልዩ ልዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሲገኝ የሚሰማውን ስሜት በስሜት ሕዋሳቱ አማካኝነት ይገልጣቸዋል፡፡ ደስታ፣ ቁጣ፣ ፍርሃት፣ ሕመም፣ ፍቅር እና የመሳሰሉት ስሜቶቻችን ናቸው፡፡ ሰው እነዚህን ስሜቶቹን በስሜት ሕዋሳቱ በዐይኑ፣ በእጁ፣ በእግሩ፣ በአንደበቱ፣ በፊት ገጽታውና በሰውነት እንቅስቃሴው ይገልጣል፡፡ እነዚህ ስሜቶች ከሚቀሰቀሱበት ሁነቶች፣ ድርጊቶችና ክስተቶች አንጻር በፍጥነት ምላሽ ሳይሰጥ ነገሮችን በዕርጋታ የሚመረምር ሰው በሳል ወይም ባለ አእምሮ ይባላል፡፡ በተቃራኒው ለጉዳዮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጠውን ደግሞ ስሜታዊ እንለዋለን፡፡ ባለ አእምሮ ሰው በመረጋጋቱ ብዙ ሲያተርፍ ስሜታዊ ሰው ግን የሚያጸጽቱና ግላዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ሀገራዊ ጥፋቶችን የሚያስከትሉ ዋጋዎችን ይከፍላል፡፡ በመሆኑም መጽሐፍ “እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ” በማለት ያስተምረናል፡፡ (፩ኛጴጥ.፬፥፯-፰) በስሜት ሕዋሳቶቻችን ለምንገልጣቸው ድርጊቶቻችንና ምላሾቻችን ጥንቃቄ እንድናደርግ ቅዱሳት መጻሕፍት በእጅጉ ያስጠነቅቁናል፡፡ ለምሳሌም ጠቢቡ ሰሎሞን “በዓይኑ የሚጠቅስ መከራን ያመጣል”፤ “ከንፈሩን የሚነ*ክስ ክፋትን ይፈጽማል” በማለት አከታትሎ የተናገራቸው ቃላት ይህንኑ ያስተምሩናል፡፡ (ምሳ.፲፥፲፣ ምሳ.፲፮፥፴) ዓይን የስሜት ሕዋስ ሲሆን ጥቅሻ ደግሞ ለአንድ ድርጊት የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡ ከንፈርን መን*ከስ የብስጭት፣ የቁጣና በአንድ ጉዳይ የመብገን ምልክት ነው፡፡ ከንፈሩን የነ*ከሰ ሰው ፈጥኖ ወደ ሕሊናው ካልተመለስ ቀጣይ እርምጃው ከንፈሩን የነከሰበትን ሰው መን*ከስ፣ ማጥ*ቃት ወይም ደግሞ አንዳች ክፉ ነገር ማድረግ ይሆናል፡፡ ስሜት በሚወልደው በአንድ ድርጊት ምክንያት የሚሰጥ ምላሽ ጥንቃቄ ካልታከለበት መዘዙ ብዙ ...